የተፃፈ መጣጥፍ

ሀምዛ ቦረና ሲከሰስ የመጀመሪያ ጊዜው ቢሆንም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ካልተገነባ የመጨረሻው ይሆናል ብሎ እንደማያምን ተናገረ::

1 Mins read

ሀምዛ ቦረና መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ.ም በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ‘ፍትሕ አዳራሽ’ ቀርቦ የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል። በ6 ክሶች የተወነጀለው ሀምዛ የእምነት ክህደት ቃሉን በሰጠበት ወቅት የሰራው ምንም ወንጀል እንደሌለና ክሱም ፖለቲካዊ እንደሆነ ከተናገረ በኃላ በተመሰረተበት ክስ ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል።

ሀምዛ በህይወቱ ሲከሰስ እና የእምነት ክህደት ቃል ሲሰጥ የመጀመሪያው ቢሆንም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ቁርጠኝነት ከሌለ ይሄ የመጨረሻው ይሆናል ብሎ እንደማያምን ተናግሯል። ቀጥሎም “በሀሰት መከሰስ እና መታሠር የሚያበቃው የፓለቲካው መንገድ የአረማመድ ሁኔታውን ሲያስተካክል ነው። ይህ ካልሆነ በዚህ ሰንካላና ኃላቀር፣ በሸርና በተንኮል የተሞላ ፖለቲካ ውስጥ ሁሌም ንፁሃን ዜጎች ሰለባ እንደሆኑና ተበዳዮች እንደ በዳይ፣ በዳዮች ደግሞ እንደተበዳይ መታየታቸው የሚቀጥል ነው። አዎ እኔም ዛሬ እዚህ ችሎት ላይ ሊያቆመኝ የቻለው ይህን ለዘመናት ሕዝቤንና አባት ታጋዮቻችንን ሲበላ የነበረ የተንኮል እና የሴራ ፖለቲካ ለመጋፈጥና ለማስተካከል የበኩሌን ድርሻ ልወጣ ብዬ ወደዚህ የፖለቲካ ዓለም ስለተቀላቀልኩ ነው። ስለዚህ በመከሰሴና በመታሰሬ አልደነገጥኩም። ቀደም ብዬ ወደዚህ የትግል መስመር ስመጣ እንደ አባቶቼ መታሰር፣ መሰቃየትና መገደል እንደምችልም አሳምሬ አውቅ ነበር። ምክንያቱም አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል በሚገባ ራሴን አዘጋጅቼ ነው የገባሁበት” ብሏል።

ሀምዛ በስደት 7 አመታት በቆየበት ወቅት ሬድዮ ዳንዲ ሀቃ (Raadiyoo Daandii Haqaa) የሚል ሚዲያ መስርቶ በዳይሬክተርነት እና በጋዜጠኝነት ህዝቡን ሲያገለግል መቆየቱን ገልጿል። በተጨማሪም “በዚህ ሬድዮ አማካኝነት የህዝቡን ትግል በሠላማዊ መንገድ ብቻና ብቻ በመምራት በአንድም ፕሮግራም ላይ ህዝብን ከህዝብ፣ አንዱን ወገን በሌላው ላይ ሳላነሳሳ በአምባገነን ሥርዓት ብቻ ላይ በማተኮር ስሠራ የነበረ ስለመሆኑ መላው ህዝብና ያኔ የተላለፉ ዝግጅቶች፣ መረጃዎች ምስክር ናቸው” በማለት ህዝብን ከህዝብ የማጋጨት ታሪክ እንደሌለው አስረድቷል።

ከአምስት ሺህ (5000) በላይ ወጣቶችን መስዋዕት አድርጎ ከመጣው ለውጥ በኃላ ወደ ሀገር ቤት መመለሱን የገለጸው ሀምዛ “የገዳ ሥርዓት ቀርፆ ያሳደገኝ ሰው ነኝና ሌሎችን ማቀፍ ደግሞ ባህላችንም ጭምር ነው” በማለት ከክሱ በተቃራኒ በብሔር ብሔረሰቦች መካከል ሰላም እንዲሰፍን ያደረገውን ጥረት ጠቅሷል። ለአብነትም ጋምቤላ ድረስ በመጓዝ በጋምቤላ ህዝቦችና በኦሮሞ ህዝብ መካከል ሠላማዊ ግንኙነት እንዲኖር፣ በአፋርና በወሎ ኦሮሞዎች መካከል የነበረው አለመግባባት በእርቅ እንዲቋጭ እና በኦሮሞና ሶማሌ ህዝብ መካከል በድንበር ምክንያት የተፈጠረው ግጭት በሰላም እንዲፈታ ስላደረገው አስተዋጾ አብራርቷል። በተመሳሳይ ሁኔታ የኦሮማራን ጥምረት መደገፉን እና በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ብሔር ተኮር ግጭቶች በተከሰቱበት ወቅት ከአማራ ክልል አክቲቪስቶች ጋር አስቸኳይ የጋራ ስብሰባ ተደርጎ ግጭቱ ወደ ህዝቡ ውስጥ እንዳይዛመት መወሰድ በሚገባቸው እርምጃዎች ላይ ውይይት የተደረገበትን መድረክ በማስተባበር ግንባር ቀደም ሚና በመጫወቱ ብዙ አደጋዎችን ለማስቀረት እንደቻለ ገልዷል።

ኦሮሞን በኦርቶዶክስ ላይ እንዲሁም በመንግሥት ላይ አነሳስተሃል የሚለው የክስ ጭብጥ ላይ አስተያየቱን ሲሰጥ ደግሞ “ስወለድ እራሴን ያገኘሁት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ሆኜ ነው” ካለ በኃላ እናት፣ አባቱ እና መላው ዘመዶቹ ኦርቶዶክስ መሆናቸውን ተናግሮ “በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ጥቃት እንዲደርስ ከቀሰቀስኩ 60 ኪሎ ሜትር ተጉዛ መጥታ እዚህ ችሎት ላይ በመታደም ላይ ያለችው እናቴ ላይ ሞት እንደመፍረድ ይሆናል” ብሏል።

ሀምዛ ሕዝብን በመንግሥት ላይ ቀስቅሰሃል የሚለውን ክስ በሁለት ደረጃዎች ከፍሎ አስተያየቱን ሰጥቶበታል። በመጀመሪያ ማለትም የለውጡ ሰሞን ህዝቡ መንግስትን እንዲደግፍ መቀስቀሱን ገልጾ ለውጡ ተቀልብሶ የኦሮሞ ብሔርተኞች እየታሠሩና እየተገደሉ ሲመጡ ወደ ተቃውሞ ለመግባት መገደዱን ተናግሯል። በመቀጠልም “የኦሮሞ ብሔርተኞች መገደላቸው ምንም ጥርጥር የለውም፤ ይህንን ብዙ [የሰብዊ መብት] ጥናቶች ያረጋግጣሉ፣ ብዙ የገበሬ ቤቶች ተቃጥለዋል። ለመሆኑ ይህንን የሚክድ አለን? ገዳዮች እያሉ እንዴት ለተበዳዮች የሚጮህ ተጠያቂ ይሆናል?” በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። አያይዞም ለሰላም ካለው ጉጉት የተነሳ በቅንነት በሥልጣን ላይ ያለውና በትጥቅ ትግል የሚፋለሙ ሀይሎች ሰላም እንዲያወርዱ ለማስቻል ወደ ደቡብ ኦሮሚያ ቦረና በመሄድ ከአባ ገዳዎች ጋር ሆኖ ለ12 ቀናት የዘለቀ ውይይትና ምክክር ማድረጉን አብራርቷል።

ከሰንደቅ አላማ ጋር ተያይዞ ስለቀረበበት ክስ ሲያስረዳ ደግሞ ህጋዊው ባንዲራ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም ያለው እና በመሀሉ የብሔር ብሔረሰቦችንና የሀይማኖቶችን እኩልነት የሚያመለክት በሰማያዊ ክብ መደብ ቢጫ ኮከብ ያለው መሆኑን አስታውሶ “እኔ በመሠረቱ በህግ፣ በህጋዊነት፣ በህገ መንግስት እና በህገ መንግሥታዊነት የማምን ህግን መከታ አድርጌ የምመለከት ዜጋ ነኝ። ከዚህ ውጪ ያለ ነገር ያስፈራኛል፤ ያሳስበኛል” ብሏል። እንዲሁም “እንደ አንድ ሠላም ወዳድና ህግ አክባሪ ዜጋ በህዝባዊ በዓላት ከብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ውጭ ሌላ ግጭት ቀስቃሽን የአንድ ቡድንን አመለካከት ብቻ የሚያመላክት ሰንደቅ ዓላማ መሠል አርማ የኢትዮጵያ እንደሆነ ተደርጎ እንዳይያዝ ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ መብቴን ተጠቅሜ ምክርና ሃሳብ ሰጥቻለሁ” በማለት ሰዎች ህጋዊውን ባንዲራ ብቻ እንዲጠቀሙ መናገር ወንጀል አለመሆኑን አስረድቷል።

ሀምዛ “የኦሮሞን ህዝብ ሲጨርስ የነበረው ነፍጠኛ ነው፤ ነፍጠኛ አይገዛንም” ብለሃል በሚል ስለቀረበበት ውንጀላ አስተያየቱን ሲሰጥ አማራና የነፍጠኛው ስርአት አንድ እንዳልሆኑና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሁለተኛ ተከሳሽ የሆነው በቀለ ገርባ የሰጠውን ማብራሪያ እንደሚቀበል ገልጾ፣ የነፍጠኛው ስርአት የአባቱን ቤተሰቦች መሬት በመንጠቅና የእናቱን ቤተሰቦች ጨፍጭፎ እንዲሰደዱ በማድረግ በደል እንደፈጸመበት ተናግሯል። በተጨማሪም “እኔ የነዚህ ተሰዳጅ፣ ተፈናቃይ ቤተሰቦች ፍሬ ነኝ። አዎ የኦሮሞን ህዝብ ሲጨርስ የነበረው ይህ የነፍጠኛ ሥርዓት ነው። ይህ ሥርዓት ዳግም እንዳይመለስ አጥብቄ ለመታገል በቂ ምክንያት የሆነኝም ለዚሁ ነው። ለመሆኑ ይህ ክፉ ሥርዓት እንዲመለስ [እኔ ነፍጠኛ ነኝ እያለ] የሚጥረው ነው ወይስ ይህ ጨቋኝ ሥርዓት እንዳያንሰራራና እንዳይመለስ የሚታገለው ነው ወንጀለኛ?” በማለት ጠይቋል።

በመጨረሻም የህዝቡን መብት ማስከበር የሚቻለው የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ በመሳተፍ መሆኑን አምኖ ወደ ኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በመቀላቀሉ ጥርስ ተነክሶበትና እሱ፣ የትግል አጋሮቹ እና ኦፌኮ በህዝብ ዘንድ ባላቸው ከፍተኛ ተሰሚነትና ተቀባይነት የተነሳ ገዢውን ፓርቲ በምርጫ እንደሚያሸንፉት ስለታወቀ ለእስር መዳረጋቸውን ተናግሯል። ይህንኑ ለማረጋገጥም “ኦፌኮን ከምርጫው ሜዳ አስወጥቶ ገዢው ፓርቲ ብቻውን ለመወዳደር እየተውተረተረ ነው” ብሏል። እንዲሁም “ሀጫሉን ገድለውብን ቀብሩን እንኳን እንዳንሄድና ለቅሶ ላይ እንዳንገኝ በሸርና ሴራ ተከለከልን። እናም ከጓዶቼ ጋር የጀግናው ሽኝትና ቀብር ላይ ስሄድ፣ ከሀጫሉ ለቅሶ ላይ ከመንገድ ታፍሰን ታሰርኩ እንጂ ምንም ወንጀል የለብኝም” በማለት ምንም የሰራው ወንጀል እንደሌለ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።