የተፃፈ መጣጥፍ

በፌደራል ፍርድ ቤት ለ3ኛ ጊዜ የተከሰሰው በቀለ ገርባ የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጠ::

1 Mins read

በቀለ ገርባ መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ.ም በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ‘ፍትሕ አዳራሽ’ ቀርቦ የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል። በቅድሚያ ብሔርን ከብሔር አጋጭተሀል በሚል ለቀረበበት ክስ ምላሽ የሰጠው በቀለ አስተዳደጉ፣ የፖለቲካ አቋሙ፣ እምነቱና ድርጊቱ ግጭትን የማያመላክት መሆኑን ገልጿል። ይህንን ሀሳብ ለማጠናከርም በኦሮሞና በጉሙዝ ህዝብ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ በነበረበት ጊዜ ከጀዋር መሀመድ ጋር ችግሩን ለመፍታት ወደ ስፍራው የሄደው በእነበቀለ ቤት ተቀምጠው አብረውት የተማሩ የጉሙዝ ብሔረሰብ አቻዎቹንና የልጅነት ጓደኞቹን አስታውሶ እንደ ነበር ተናግሯል። በስራ አጋጣሚ ወደ ጌዴኦ በሄደበት ወቅትም ለህዝቡ ካለው ክብር የተነሳ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ቋንቋቸውን ለምዶ ያለ አስተርጓሚ ህዝቡን ማገልገሉን አስረድቷል። አክሎም “በፖለቲካ አስተሳሰቤ በዴሞክራሲና በውይይት የማምን፣ በትግል ስልት የነማህተመ ጋንዲ ሳትያግራሀና የማርቲን ሉተር ኪንግ የሰላማዊ ትግል ተከታይ ነኝ። የሰው ልጅ መመዘን ያለበት በቆዳ ቀለሙ ሳይሆን በባህሪው መሆን እንዳለበት ‘ህልም አለኝ’ በሚለው ዝነኛ ንግግሩ አስረግጦ የተናገረውን ታዋቂ የሲቪል መብት ተሟጋች ማርቲን ሉተር ኪንግ መጽሀፍ ወደ አማርኛና አፋን ኦሮሞ በመተርጎም እኛም ሰውን የምንለካው በብሔሩ ሳይሆን በግል ባህሪው መሆን እንዳለበት ትምህርት እንድንቀስምበት ለማድረግ ሞክሬያለሁ” ብሏል።

በአጠቃላይ ወደ ፖለቲካው ከመግባቱ በፊትም ሆነ ከገባ በኋላ አንድም ቀን በንግግርም ይሁን በጽሑፍ የየትኛውንም ብሔር ክብር ዝቅ የሚያደርግ ወይም የሚያንቋሽሽ ተግባር ፈጽሞ እንደማያውቅ እና ይህንን ማንም ሊያረጋግጥበት እንደማይችል ለፍርድ ቤቱ አሳውቋ። በተጨማሪም “እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ በሀሰት ስሙ እንደኔ የጎደፈ የጥላቻ ዘመቻ የተደረገበት መኖሩን እኔ አላውቅም” በማለት የተመሰረተበት ክስ ሀሰተኛ መሆኑን ገልጿል።

በመቀጠል ህዝብን በመንግስት ላይ አነሳስተሀል የሚለው ክስ ላይ አስተያየቱን የሰጠው በቀለ በአገራችን በየጊዜው ከተፈራረቁ መንግስታት ባህሪ የተነሳ መልካም ግንኙነት እንዳልነበረው ገልጾ “በዚህ ፌደራል ፍርድ ቤትም ይኸው ለሶስተኛ ጊዜ ቀርቤያለሁ” ካለ በኃላ የመሬት ወረራና የገበሬዎች መፈናቀልን በማስመልከት ከረር ያለ ትችት ማቅረቡ ለእስር ከዳረጉት ምክንያቶች አንዱ እንደነበር በማስታወስ “ያኔ ያደረግኩት ህዝብን በመንግስት ላይ ማነሳሳት ሆኖ ከተቆጠረ አዎ አድርጌያለሁ” ብሏል። በተጨማሪም በስልጣን ላይ ያሉት አካላት የህዝቡ ጫና ሲበረታባቸው “አሸባሪዎች እኛ ነን፣ ህዝቡ ስህተት የለበትም፣ በደል አድርሰናል፣ ሰርቀናል ብለው መናገር በመጀመራቸው ይህንኑ ፍርድ ቤት መጥተው እንዲመሰክሩልን የአሁኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣኖችን በመከላከያ ምስክርነት ጠርተን በቀጠሮ ላይ እንዳለን ፓርቲው በውስጡ ባደረገው ሽግሽግ በወቅቱ ከፍተኛ ነው የተባለ ለውጥ ተደርጎ የእኛም ክስ ተቋርጦ ከእስር ቤት ወጣን” በማለት ተናግሯል።

በቀለ በወቅቱ ለውጡን ከመደገፍ አልፎ ሌሎችም እንዲደግፉት ያደረገውን ጥረት በመዘርዘር በለውጡ ተስፋ ማድረጉን “የዋህነት ነበር” በማለት በማለት ገልጾታል። እንዲሁም “በአጠቃላይ ለውጡ እንዲህ በፍጥነት ሀዲዱን ይስታል ብዬ አልገመትኩም ነበር። ሺዎች በወጡበት እስር ቤት አስር ሺዎች ይገባሉ ብዬ አላሰብኩም። አንድ ማዕከላዊ ተዘግቶ ት/ቤቶች ሁሉ ማዕከላዊ ይሆናሉ ብዬ አልገመትኩም። ባዶ እጃቸውን ታንክ ፊት ቆመው የታገሉ ወጣቶች ሸኔ ተብለው ተገድለው ይህን ያህል ደመሰስን ተብሎ እንደ ጀብድ በሚዲያ ይታወጃል ብዬ አልገመትኩም። የኦሮሞ እናት ዳግም ታለቅሳለች ብዬ እንደምን አስባለሁ? እዚሁ አገር ያለ የመከራ ገፈት ቀማሽ ምሁር እያለ ዲያስፖራው እየበረረ መጥቶ መሬት እየተቀራመተ ስለ ትግል ያስተምራል ብዬ ከቶ አላሰብኩም ነበር። የገበሬ ቤት እያቃጠለ ከቦ የሚጨፍር የመንግስት ታጣቂ ይኖራል ብዬ እንዴት ልገምት እችል ነበር?

ገዢው ፓርቲ ለሁለት ተገምሶ ወታደሩ እርስ በራሱ ተዋግቶ መከላከያችን ተዳክሞ በሮቻችን ለባዕዳን እንዲህ ወለል ብለው ይከፈታሉ ብዬ እንዴት እገምታለሁ? ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተፎካካሪ ናችሁ ተብለን ቢያንስ በስያሜው ተደስተን ሳንጨርስ ጽፈት ቤቶቻችን በሙሉ ተዘግተው፣ አባሎቻችን በሙሉ ታስረው፣ ከምርጫ እንወገዳለን ብለን ፈጽሞ አላሰብንም። ዘጠና ከመቶ በላይ የመንግስትና የግል ሚዲያዎች በአንድ ብሔር ቁጥጥር ስር ሆነው በሌሎች ላይ ይዘምታሉ ብዬ አልገመትኩም ነበር። ጭካኔንና ሬሳ መቁጠርን እንለማመዳለን ብዬም አላሰብኩም። በአጠቃላይ እውነትና ውሸት ባልተጠበቀ ፍጥነት ቦታቸው ተቀያይሮ ሁሉ ነገር (ሥልጣን፣ ሀብት፣ እውቀት፣ እምነትና ተቋም) ክብር ሲያጣ ዝም ብዬ ማየት ባለመቻሌ የማሰማው ተቃውሞ መንግስት ላይ እንደማነሳሳት ተቆጥሮብኝ ሊሆን ይችላል። እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ተደራጅተን፣ ህጋዊ ፈቃድ አውጥተን የምንንቀሳቀሰው እንዲህ አይነቶቹን እኩይ የመንግስት ተግባራት በመጠቆም፣ ለህዝብ በማሳወቅ፣ በይፋ በማጋለጥና በመተቸት እንዲታረሙ በሰላማዊ መንገድ ጫና ለመፍጠር ነው። እንደ አንድ ዜጋና አንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር እነዚህ ተግባራት መብቴ ብቻ ሳይሆኑ ግዴታዎቼም ናቸው” ብሏል።

በቀለ የመንግስት የስልጣን ዘመኑ መስከረም 30 ያበቃል በማለት ቀስቅሰሀል በሚል ለቀረበበት ክስ ደግሞ ህገ-መንግስቱ የቃልኪዳን ሰነዳችን እንደሆነ፣ ማንም እንደፈለገው የሚጥሰው መሆን እንደማይገባውና የተጻፈውም በዋነኝነት ለአምባገነን መሪዎች ልጓም እንዲሆን ታስቦ እንደሆነ አብራርቷል። እንዲሁም ህገ-መንግስቱ በስልጣን ላይ ያለው አካል ከአምስት አመት በላይ ለመቆየት የሚያስችለው ምንም ክፍተትና ትርጉም በማያስፈልገው መልኩ መደንገጉን ገልጿል። ነገር ግን ገዢው ፓርቲ ስልጣኑን ለመልቀቅ ባለመፈለጉ ከራሱ ፓርቲ ብቻ የተውጣጡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ትርጉም በማያስፈልገው ህገ-መንግስታዊ ጉዳይ ላይ ትርጉም እንዲሰጡ በማድረግ በህገወጥ መንገድ የስልጣን ጊዜውን ማራዘሙን ለፍርድ ቤቱ አብራርቷል። ቀጥሎም “ዛሬም ቢሆን አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ስልጣኑን ህገ-መንግስታዊ ባልሆነ መንገድ በህገወጥነት ይዞ የቀጠለ ነው የሚል እምነት አለኝ። ይሄ ሊያስከስሰኝ አይችልም። ይልቅ መክሰስ ያለብኝና መካስ የነበረብኝ እኔ ነበርኩ” ብሏል።

የኦሮሞን ህዝብ ሲገድል የነበረው ነፍጠኛ ነው፣ በነፍጠኛ ስርአት ስር መተዳደር የለብንም ብለሀል በሚል ለቀረበበት ክስ ደግሞ “የነፍጠኛው ስርአት ይህን አላደረገም የሚል ካለ ይህ ያለንበት ስፍራ ፍርድ ቤት አይደለም ሊል ስለሚችል ለመግባባት እንቸገራለን” በማለት ምላሽ ሰጥቷል። አያይዞም “ነፍጠኛ ማለት ነፍጥ ይዞ የአንድን አካባቢ ህዝብ ወርሮ፣ የገደለውን ገድሎ፣ መሬቱን በጉልበት ቀምቶ፣ የቀረውን አስገብሮ፣ ቋንቋውን ባህሉንና እምነቱን ያለፍላጎቱ ጭኖበት የሚገዛው ገዢ መደብ ነው። ታዲያ ይህንን ስርአት ያልታገሉ ምንን ይታገላሉ? ይህን በመሰለ ሰርአት ስር ለመተዳደር ፍቃደኛ አለመሆን ምን ያስከስሳል? እኔ አሁንም በእንዲህ አይነት ስርአት ስር መተዳደር አልፈቅድም” በማለት ተናግሯል።

በመቀጠልም በክሱ ውስጥ ነፍጠኛና አማራን ሆን ብሎ በማምታታት በመቅረቡ የሁለቱን ልዩነት በሰፊው አብራርቷል። ምንም እንኳን ነፍጠኝነት ከመሬት ስሪት ጋር የተያያዘ በመሆኑ እንደ ስርአት የካቲት 1967 በታወጀው የገጠር መሬት አዋጅ መሰረት ቢነቀልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአስተሳሰብ ደረጃ አቆጥቁጦ በኢትዮጵያ አንድነት ሽፋን የራሳቸውን ማንነት ብቻ የአገሪቱ ነጸብራቅና ወካይ በማድረግ የሌላውን ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነትና ታሪክ በአጠቃላይ ብዝሀነትን አናንቆ እንደ ዘረኝነት በመቁጠር ህዝቦችን ማሸማቀቅ እየጎላ መምጣቱን መታዘቡን ገልጿል። እንዲሁም “ይባስ ብሎ አለም እንደ ጸያፍና አሳፋሪ ታሪክ በመቁጠር ህዝቦችን ይቅርታ የጠየቀበትን ስርአት ከተቀበረበት ጉድጓድ አውጥቶ እንደ አኩሪ ታሪክ በመቁጠር “የነፍጠኛ ልጅ ነኝ” የሚል ቲሸርት በመልበስ መንጎማለል ተጀምሯል” ካለ በኃላ “ዘመናዊው የነፍጠኝነት አስተሳሰብ የሚቀነቀነው በበርካታ ዘርፎች ሲሆን ዘመቻው የሚካሄደው በመንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ ባሉ የዚህ አስተሳሰብ ሰለባ የሆኑ ሰዎች፣ በመንግስትና በግል ሚዲያዎች፣ በአክቲቪስቶች፣ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ነን በሚሉ ግለሰቦች፣ በሲቪክ ማህበራት፣ በገጣሚያንና በደራሲያን፣ በምሁራንና በተመራማሪዎች፣ በኮሜዲያኖች እና በስፖርት ደጋፊዎች ስም በአገር አንድነት ጭምብል ነው” በማለት አስረድቷል።

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሁለት ጎራዎች እንደተከፈለ የተናገረው በቀለ አንደኛው ወገን የተለያዩ ተቋሞችን በመጠቀም ህብረ ብሄራዊ ፌደራሊዝሙን በማፍረስ፤ ህገ-መንግስቱን በመለወጥ የቀድሞውን ስርአት (የአንድን ወገንን ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ) የበላይነት ለማስፈን የሚፈልግ ሲሆን በሌላ በኩል ብዝሀነትን የሚያስተናግድና የሚያከብር ስርአት በሂደት እየጎለበተ እንዲሄድ የሚፈልግ ጎራ መኖሩን ጠቁሟል። በመጨረሻም “የቀደመው ጎራ ተቋሞቹን ሁሉ አጠናክሮ መጠነ ሰፊ ዘመቻውን በማፋፋም የኃለኞቹን በሰበብ አስባቡ ከፖለቲካው ሜዳ ውጪ እንዲሆኑ በማድረግ ለብቻው በምርጫ በመወዳደር አላማውን ለማስፈጸም እየተጋ ነው። ለዚህም የሀሰት ክስ ፈጥሮ ወደ ግቡ እየገሰገሰ ነው። ክሱ የፈጠራ ነው። አላማው ፖለቲካዊ ነው። የፈጸምኩት ወንጀል የለም። የብርቅዬ ልጃችን አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን አስክሬን ለመሸኘት በቀብር ስነስርአቱ ላይ ለመገኘት ያደረኩት ሙከራ እንደ ወንጀል የሚቆጠር ከሆነ ደግሞ ዘላለም ብታሰር አይቆጨኝም” በማለት የቀረበበት ክስ ላይ የሰጠውን አስተያየት አጠናቋል።